መልስ ለጥያቄዎቻችሁ

ጥያቄዎቻችሁን ለላካችሁልኝ ሁሉ እያመሰገንኩ እዚሁ መልስ ለመስጠት ሞክሪያለሁ። ሌሎችም ጥያቄዎቻችሁን ላኩልኝ። በገባኝ ልክ መልሶቹን ለማቅረብ እሞክራለሁ።

ከዚህ በታች ያሉትን ጥያቄዎች click  በማድረግ መልሶቹን ማንበብ ትችላላችሁ።

 

ጥያቄ፡

አሰላሙ አለይኩም

የእኔ ጥያቄ የግድ  ህልም ማስቀመጥ ያስፈልገኛል ወይ? የሚል ነው። አመሰግናለሁ።

መልስ፡

ወዓለይኩሙሰላም ወረሕመቱላሂ ወበረካትሁ።

በዘልማዳዊው (Traditional) የአኗኗር ሂደት ግልፅ የሆነ ህልም ሊኖርህ ግድ አይደለም።

  • ትወለዳለህ
  • ታድጋለህ
  • ‘የመሰለህን’፣ ወይም ‘የገጠመህን’፣ ወይም ‘የተሳካልህን’ ትማራለህ
  • ‘የመሰለህን’፣ ወይም ‘የገጠመህን’፣ ወይም ‘የተሳካልህን’ ስራ ትሰራለህ
  • ‘ቀኑ እንዳዋለኝ’ እውላለሁ ትልና ቀኑ ‘እንዳዋለህ’ ትውለዋለህ
  • መንገዱ ወደ ወሰደህ ትሄዳለህ
  • ታረጃለህ
  • የተፈቀደልህ ጊዚ ያልቃል።

ይሄ የህይወት ዓላማ ሳይኖርህ መኖር ነው። ህልም ማለት የህይወት ዓላማህን የምታሳካበት ራዕይህ ነው።

ስለዚህ ህልም የሚያስፈልገው የህይወት ዓላማህን ለማሳካት ነው።

የህይወት ዓላማ ሲባል ግን ምን  ማለት ነው?

እንዲህ ብናየውስ፡

የተፈጠርንበት ዓላማ አላህን ለመገዛት ነው።

ዒባዳ ሲባል ደግሞ በብዙ መንገድ ነው። ከፈርዶቹ ባሻገር የዒባዳ ዘርፉ ብዙ ነው። ዋናው አላህ ያዘዘውን መስራት፣ የከለከለውን መከልከል ነው። ይህ ብቻ ግን አይደለም። አላህ የሚወደውን ማድረግ፣ አላህ ከሚጠላው መራቅም ዒባዳ ነው። የህይወት ዓላማህ በዚህ የተቃኘ ሊሆን ይገባል። ህልምህ ደግሞ የህይወት ዓላማህን ለማሳካት የምትጠቀምበት ራዕይህ ነው።

ይህን በምሳሌ እናብራራው፡

በእሰልምና ተወዳጁ ሰጪ መሆን እንጂ ተቀባይ መሆን አይደለም። ቢያንስ ራስህን መቻል፣ ከሰው አለመጠበቅ፣ ከቻልክ ደግሞ ለሰው መትረፍ።

አላህ ከሚያዛቸው ወይም ቢያንስ ከሚወዳቸው ነገሮችና በዒባዳነት ከሚጠቀሱት ጥቂቶቹን ብንወስድ፡

ሰደቃ ማውጣት፣ ዘካ ማውጣት፣ ሃጅ ማድረግ፣ መስጊድ መስራት (ማሰራት)፣ ማግባት፣ መውለድ፣ ልጆችን በአግባቡ ማሳደግ፣ ወላጆችን መንከባከብ፣ ዘመዶችን መርዳት፣ ጎረቤቶችን ማገዝ፣ የቲሞችን መርዳት፣ ለዲንህ፣ ለዑማህ፣ ለሃገርህ በበጎ አስተዋፅኦ ማድረግ፣ በሞያህ ሰዎችን መርዳት፣ ለሰዎች የሚጠቅሙ ስራዎችን መስራት፣ የታመመ መጠየቅ፣ ማሳከም፣ ዱዓ ማድረግ፣ ሆስፒታሎችን መገንባት፣ የዉሃ አቅርቦት መገንባት፣ ኢስላማዊ የእውቀት ማዕከላትን መገንባት፣ ወዘተ. ሊሆኑ ይችላሉ።

ከነዚህ የተወሰኑትን እንኳን ለማሳካት የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የጊዜ፣ የእውቀት፣ ወዘተ. አቅም ማዳበር አለብህ። እነዚህን አቅሞች አዳብረህ ከላይ የተጠቅሱትን ዓላማዎች ለማሳካት አስበህ አቅደህ በቁርጠኝነት ተነስተህ የምታስቀመጠው ራዕይ ደግሞ ህልም ይባላል። 

ህልም ከሌለህ ‘መንገዱ በወሰደህ ሄደህ እንዳዋለህ ትውልና’ ሰበበኛ ትሆናለህ። አቅሙ ሰላልነበረኝ ማድረግ አልቻልኩም! ይሆናል መልስህ። ግን አሰታውስ አላህ በሰራሃቸው ስራዎች እንደሚከፍልህ ሁሉ በሰጠህ አቅምም ይተሳሰብሃል። ወጣትነት ሰጥቶህ ካልተጠቀምክበት ይተሳሰብሃል፣ ጊዜህን ይተሳሰብሃል፣ ወዘተ. የምታስብበት አእምሮ ሰጥቶሃል፣ ዓፊያ፣ ጉልበት፣ ወዘተ ሰጥቶሃል።

እነዚህን ሁሉ አቅሞች ተጠቀምና ትልቅ ህልም አስቀምጥ፣ ትልቅ ስራ ስራ። እውቀትን ፈልገህ አግኝና አላህ የሚወዳቸው ትልልቅ ስራዎች ስራበት፣ ሪዝቅ በሃላል ፈልገህ አግኝ፣ ሃበታም ሁንና አላህ የሚወዳቸውን ስራዎች ትሰራበታለህ። ዘካ ታወጣበታለህ፣ ሰደቃ ታወጣበታለህ። ሰዎችን ትረዳበታለህ፣ ሃጂ ታደርግበታለህ፣ ትዳር ትይዝበታለህ ልጆችህን በአግባቡ ታሳድግበታለህ፣ ወላጆችህን ትንከባከብበታለህ፣ ለዑማው የሚጠቅም ስራ ትሰራበታለህ፣ መድረሳዎችን ታሰራበታለህ፣ እውቀት ታስፋፋበታለህ፣ ወዘተ. 

ገንዘብ ካልሆነ ፍላጎትህ ደግሞ እውቀት ወይም ሞያህን ለማሳደግ ህልም ይኑርህ። ሃኪም ሆነህ ሰው ትረዳለህ፣ ወይም ሃፊዘል ቁርአን ትሆናለህ፣ ወይም ኢስላማዊ እውቀትህን አዳብረህ (ዓሊም ሆነህ) እውቀትን ለትውልድ ታስተላልፋለህ። ፍላጎትህ በየትኛውም ዘርፍ ይሁን ህልም ይኑርህ። 

ሲጠቃለል፡

የተለየ ህልም መኖር የግዴታ መስፈርት ባይሆንም፣ የህይወት አላማህን ለማሳካት አቅጣጫ እንዲኖርህ የሚያደርግ ነገር መኖሩ አስፈላጊ ነው።

© ሙስጠፋ አብደላ

ሙስጦፋ እንዴት ነህ?

እኔ እስካሁን ህልሜን አላገኘሁም። ብዙ የማስባቸው ነገሮች ቢኖሩም ህልሜ የምለውን ግን ማግኘት አልቻልኩም። ህልሜን እንዴት ላግኝ? ነው የኔ ጥያቄ። አመሰግናለሁ።

መልስ፡

እኔም አመሰግናለሁ።

በህይወት ውስጥ ትልቁ ህልምህ ምን እንደሆነ ማወቅ ፈታኝ እና አንዳንዴም የእድሜ ልክ ጉዞ ሊሆን ይችላል። ትልቁን ህልምህን ለመለየት እና ለማግኘት እንዲረዳህ ሁለቱ መነሻ መንገዶች እንያቸው።

1.    አንደኛው መንገድ ካለህ Resource ወይም ካለህ ሃብት ተነስተህ የምታስበው ነው። ሃብት ሲባል የግድ ቁሳዊ ሃብት ወይም የገንዝብ አቅም ብቻ አይደለም።

1.1.  የምትችለው ሙያ ምንድነው?

1.2.  የትምህርትህ Background ምን ላይ ነው

1.3.  የስራ ልምድህ ምን ላይ ነው

1.4.  በደምብ የምትችለው ስራ ምንድነው

1.5.  የምትወደው ስራ ምንድ ነው

1.6.  ባለህ ነገር ልትሰራቸው የምትችላቸው ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?

እነዚህን ስታስብ በቂ መስለው ካልታዩህና ህልም ለማስቀመጥ መነሳሳት ካቃተህ ወረቀት እና እስክርቢቶ ያዝ እና አላህ የሰጠህን ኒዕማዎች ዘርዝረህ ለመጻፍ ሞክር። ዘርዝረህ አትጨርሳቸውም። ግን የቻልከውን ጻፍ።

ወጣትነትህ፣ ኢነርጂህ፣ አእምሮህ፣ የትምህርት ደረጃህ፣ እውቀትህ፣ ያለህ መነሻ ገንዘብ፣ ወላጆችህ፣ ወንድም እህቶችህ፣ ጓደኞችህ፣ የቅርብህ ሰዎችህ፣ ሰላምህ፣ ወጥቶ መግባት መቻልህ፣ ያለህ የንግድ ይሁን የሌላ የስራ ልምድ፣ ዘመዶችህ፣ ዲንህ፣ ዒልምህ፣ ታለንትህ፣ ጤንነትህ፣ ጉልበትህ፣ የቋንቋ ችሎታህ፣ የንግግር ችሎታህ፣ የመግባባት ችሎታህ፣ ባህሪህ፣ ታማኝነትህ፣ ያሉት የገበያ እድሎች፣ ወዘተ. እነዚህ ሁሉ አላህ የሰጠህ ኒዕማዎች ናቸው።

ከነዚህ ተነስተህ የእድገት ሃሳብ ታመነጭና ያለህን ቁሳዊም ሆነ አእምሯዊ ሃብት በማሳደግ ወድምትፈልገው የስኬትና የእድገት ደረጃ ለመድረስ መድረሻህን በምናብህ ትሰልዋለህ (Imagine ታደርገዋለህ)። በምናብህ ስታየው የሚፈጥርብህ ስሜት፣ የሚጨምርልህ ኢነርጂ፣ ወዘተ.  በማየትና ውስጥህን በማንበብ የህልምህን ፍንጭ ልታገኝ ትችላለህ።  

2.    ሁለተኛው መንገድ ከውስጣዊ እውነተኛ ስሜትህ በመነሳት የምታስበው ነው። ሁሌ ባሰብከው ቁጥር ስሜትህን የሚቆጣጠረው፣ ከፍተኛ መነሳሳት የሚፈጥርብህ፣ ኢነርጂህን ከፍ የሚያደርግልህ፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን እንኳ ማንኛውም መስዋእትነት ከፍለህ ልታሳካው ፈቃደኛ የምትሆንበት ሆኖ የሚሰማህ ነገር ካለ ትልቁ ህልምህ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ይሰጥሃል። 

ሲጠቃለል ከሁለቱ በየትኛውም ተነሳ ዋናው ነገር ህልምህ ማለት ተነሳሽነትህን ፣ ፈቃድህን እና ጽናትህን የሚያጎላ  የወደፊቱን እያሰብክ የምትነቃቃበት ምስል ነው። ህልምህን ለማሳካት የምትችለውን ሁሉ እንድታደርግ በአእምሮህ የምትቀርጸው ምስል ራሱ ኃይል  ይሰጥሃል።

ህልምህ አላማህንና አቅምህን የምትመለከትበት ምስል (blueprint) ነው። ትክክለኛ ህልምህ መሆኑን የምታውቀው ግን ለስኬቱ ምን ያህል መስዋእትነት ልትክፍልለት ዝግጁ እንደሆንክ ውስጥህን በማዳመጥ ነው። ትክክለኛ ውስጥህን የምታዳምጠው ደግሞ ኢነርጂህ በጣም ደክሞ ስሜትህ በወረደበት ወይም ኢነርጂህ በጣም ከፍ ብሎ ስሜታዊ በሆንክበት ጊዜ ሳይሆን አእምሮህ በመረጋጋት ውስጥ ሲሆን ነው።

ስለዚህ መጀመሪያ የአእምሮ ውጥረትን አስውግድና ውስጥህን አረጋጋው። የዛኔ ሁሉም ነገር ፍንትው ብሎ ሊታይህ ይጀምራል።

© ሙስጠፋ አብደላ

ጥያቄ፡

አሰላሙዓለይኩም። አስቀደሜ አመሰግናለሁ።

ባለፈው የላኩትን ጥያቄ ግን እስካሁን አልመለስክልኝም።

የአሁኑ ጥያቄዬ እንደዚህ ነው።

ህልሜን አግኝቻለሁ። ማለት ለይቼ እውቄዋለሁ። ግን በተግባር እንቅስቃሴ መጀመር አልቻልኩም።እንዴት ደፍሬ እንደምጀምረው እንድትነግረኝ ብዬ ነው።

መልስ፡

ወዓልየኩሙሰላም ወረሕመቱላሂ ወበረካትሁ

በመጀመሪያ ህልምህን ለይተህ በማግኘትህ እንኳን ደስ አለህ! ይህንን ለማሳካት ጉዞህን ለመጀመር እነዚህን ነጥቦች መከተል ትችላለህ፡

  • በመጀምሪያ የአእምሮ ውጥረትን አስወግድ። ይህን ስታደርግ አእምሮህ መረጋጋት እና አዳዲስ ሃሳቦችንና መፍትሄዎችን ማፍለቅ ይጀምራል። ልብ በል ብዙ እድሎች አጠግብህ እያሉ የሚጋረዱብህ አእምሮህ ሁሌም ውጥረት ውስጥ ስለሚሆን ነው። (የአእምሮ ውጥረትን እንዴት ላስወግድ ለሚለው ጥያቄ መልሱ በሌላ ጥያቄ መልሼዋለሁ)
  • በመቀጠል የ Procrastination ፓራዳይምህን አስወግድ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች አዲስ መንገድ፣ አዲስ ስራ እንዳይጀምሩ ወይም የለውጥ ጉዞ ውስጥ እንዳይገቡ ከሚያግዷዋቸው ነገሮች ዋነኛው Procrastination ነው።
  • ልዩ፣ ሊለካ የሚችል፣ ሊደረስ የሚችል፣ ተዛማጅነት ያለው እና በጊዜ የተገደበ (SMART) ግቦችን አውጣ፡ ህልምህን ለማሳካት የሚረዱህ የተወሰኑ ግቦችን ግለጽ። እነዚህ ግቦች ተጨባጭ፣ የሚለኩ እና የጊዜ ገደብ ሊኖራቸው ይገባል።
  • ግቦችህን ለማሳካት መውሰድ ያሉብህን እርምጃዎች የሚገልጽ ዝርዝር እቅድ ያዝ። ይህ እቅድ የተወሰኑ እርምጃዎችን፣ የጊዜ ሂደትን እና አስፈላጊ ግብአቶችን ማካተት አለበት።
  • ግቦችህን ለማሳካት እርምጃ መውሰድ ጀመር። እዚህ ላይ ለመጀመር ስትፈልግ ትንሽ እና ቀላል በሆነችዋ ስራ ጀምር። ይህም Procrastinationን ለመከላከል እና ደረጃ በደረጃ ኢነርጂህን ለመገንባት ይረዳሃል።
  • በጣም ወሳኝ በሆኑ ደረጃዎች ላይ በማተኮር ጀምር። ከዛ ፍጥነትህን ቀስበቀስ ጨምር።
  • ትኩረትህ የመጨረሻ ስኬትህ ላይ ይሁን። የሂደቱን ውስብስነትና አስቸጋሪነት እያሰብክ ራስህን አታድክም።
  • ተነሳሽነት ይኑርህ፡ የራስህን ሞራል በመገንባት፣ የህልምህን የመጨረሻ ስኬት ደጋግመህ በማሰብ እና ስኬቶችህን ቀድመህ በሃሳብህ በማጣጣም ራስህን አነሳሳ። (Imagination የሚጠቅምህ እዚህ ላይ ነው።)
  • ድጋፍ የምታገኝበት እድል ካለ ከመጠቀም ወደኋላ አትበል። ግን ሙጭጭ አትበል። ምክንያቱም የተረጂነት ስሜት እንዳይሰማህና ኢነርጂህ እንዳይቀንስ። ምክር እና ማበረታቻ ከሚሰጡ ቤተሰብ፣ ጓደኞች፣ አማካሪዎች ወይም ባለሙያዎች ድጋፍ ብታገኝ ተጠቀምበት።
  • ያለማቋረጥ ገምግም እና አስተካክል፡ ወደ ግቦችህ ያለውን ሂደት ያለማቋረጥ እየገመገምክ እንደ አስፈላጊነቱ እቅድህን አስተካክል።
  • ህልምህን ለማሳካት፡ ጊዜ፣ ጥረት እና ፅናት የሚጠይቅ ጉዞ መሆኑን አስታውስ። ታጋሽ ሁን፣ ቁርጠኝነት ይኑርህ።
  • ህልምህ በእርግጠኝነት እንደምታሳካ ያለህ እምነት መቼም እንዳይጎድል ተጠንቀቅ። ምክንያቱም እምነትህ በጎደለ ቁጥር አንድ እርምጃ ወደኋላ ይመለስሃል።

© ሙስጠፋ አብደላ