‘ጭንቅላትህ ውስጥ የፈለግከውን ማድረግ የሚያስችልህ ትልቅ ሃይል አለ’ ይላል ሳይንሱ። ታዲያ በምትፈልገው ነገር ስኬታማ እንዳትሆን ምንድነው የሚያግድህ?
ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋናው ግን ትኩረት አልባ መሆን ነው። ምን ማለት ነው?
እስቲ እንደዚህ እንየው። ጥዋት ግቢ ውስጥ ቁጭ ብለን ጸሃይ እንሞቃለን። ምናልባትም ለሰአታት ጸሃዩ ብዙም ሳያቃጥለን ልንቆይ እንችላለን። ይህ የሆነው የጸሃይ ብርሃኑ ተበትኖ ስለሚመጣ ነው። converging lens ተጠቅመን የጸሃይ ብርሃኑን ወደ አንድ ነጥብ ብንሰበስበው ግን እሳት ልናቀጣጥልበት የምንችልበት ያህል ብርታት ይኖረዋል። ይህም የሚሆነው የብርሃን ሃይሉ ወደ አንድ የስበት ማእከል (Focal point) ስለሚሰበሰብ ነው።

በተመሳሳይ የአእምሮህን ሃይል ወደ አንድ የስበት ማእከል ብትሰበስበው የምትፈልገውን ተአምር መስራት ትቸላለህ።
ውይይታችን ስለ ቢዝነስ ስለሆነ ወድዛ እንመለስ።
ቢዝነስህን ስፔሻላይዝ ማድረግ ማለት አንድ መስራት የምትፈልገውን ቢዝነስ መርጠህ የስበት ማእከልህ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው። በዚህም የአእምሮህን ተአምራዊ ሃይል በዚህ በምትፈልገው ቢዝነስ ላይ ብቻ በማሳረፍ የምትፈልገው ስኬት ላይ በቀላሉ መድረስ ትችላለህ።
የBusiness Specialization መንገድ የምትጠቀም ከሆነ አንድ ቢዝነስ ላይ ብቻ አተኩረህ ትሰራለህ ማለት ነው። በቢዝነስህ ላይ፡ ሙሉ ትኩረት፣ ጥልቅ እውቀት፣ የተሻለ ልምድ፣ ሙሉ የአቅም አጠቃቀም (Full Resource Utilization) ፣ ሙሉ የጊዜ አጠቃቅም ይኖርሃል። በዚህም በተከፋፈለ ትኩረት ከሚሰሩ ተፎካካሪዎችህ እጅግ በተሻለ እድል ለስኬት ትቀርባለህ ማለት ነው።
ለምሳሌ የግብርና ምርቶች አቅራቢ ብትሆን እና በዚህ ቢዝነስ ላይ ብቻ አተኩረህ የምትሰራ ከሆነ በዚህ ቢዝነስ ላይ ሙሉ አትኩሮት ስለሚኖርህ በማንኛውም መስፈርት በተደራቢነት ቢዝነሱን ከሚሰሩት ሰዎች የተሻለ የስኬት እድል ይኖርሃል።

ይህ እስካሁን ያየነው Specialized Business ይሻላል የሚሉ ሰዎች መከራከሪያ ሃሳብ ነው።
በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ Generalized Business ይሻላል የሚሉ ሰዎች መከራከሪያ ሃሳብ እናቀርባለን። ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ወይም ጥያቄ ካላችሁ ከታች ኮሜንት መጻፊያው ላይ መጻፍ ትችላላችሁ። ለተሳትፏችሁ እናመሰግናለን።
© ሙስጦፋ አብደላ


Add a Comment