322195384_2394257100743680_5599242843199550230_n

ድንቅ ሃሳብ ዋጋው ስንት ነው?

ስለቢዝነስ ፈጠራ የጀምርኩላቸሁን ወሬ ለመቀጠል ሳስብ አንድ ከዚህ ቀደም ያነበብኩት ነገር አስታወስኩ። በጣም ጠቃሚ ሃሳብ ነው። ያንን መንገድ ተከትላችሁ ከሂዳችሁ ህይውታቸሁ ተለውጦ ታገኙታላቸሁ። እንዴት እንደሆነ ዝርዝሩን ሌላ ጊዜ አካፍላችኋለሁ። አሁን ግን ሃሳቡን ባጭሩ ልግለፅላችሁና በሃገራችን በዚህ መንገድ ተጉዘው ውጤታማ ከሆኑ ጀግና ኢንተርፕረነሮች አንዷ ስለሆነችው ሴት እና ስለስራ ፈጠራዋ ማህበራዊ ጠቀሜታ ትንሽ ልበል።

መጀመሪያ ስለ ሳይንሳዊው አስገራሚ ራስን በአጭር ጊዜ የመቀየሪያ ዘዴ ልንገራችሁ።ያነበብኩት ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡ “Stop Chasing Money; Chase Problems and Find Solutions to those Problems”. “ገንዝብ ማሳደድህን አቁምና ማህበራዊ ችግሮችን አሳድደህ መፍትሄ ፈልግ”። ያንተን ለውጥ የሚወስነው የመፍትሄው ዋጋ ነው። የ1ሚሊዮን መፍትሄ ካመጣህ አንድ ሚሊዮን ታገኛለህ። የ100 ሚሊዮን መፍትሔ ካመጣህ 100 ሚሊዮን ታገኛለህ። መፍትሔው ብዙ ሰዎችን የሚጠቅም ከሆነ ብዙ ትጠቀማለህ። ጥቂት ሰዎችን ታሳቢ ያደረገ ከሆነ ትንሽ ጥቅም ታገኛለህ። ስለዚህ አንተ ታላቅ ሰው ነኝ ብለህ ራስህን አሳምንና ለትልቅ ችግር ታላቅ መፍትሄ ፈልግ። ወይም ሚሊዮኖችን የሚጠቅም መፍትሔ ፈልግና ሚሊየነር ሁን። ለዚህ ቀላል ምሳሌ የሚሆነው የፌስቡክ ፈጣሪው ማርክ ዙከርበርግ ነው። ቢሊዮኖችን የሚጠቅም አንድ መላ ፈጠረ፣ ቢሊየነር ሆነ። በቃ።

ወደ ሃገራችን መለስ ብየ ለማሰብ ሞከርኩ። ብዙዎችን መጥቀስ እችላለሁ። ነገር ግን ቀድማ የመጣችልኝ በሆነ አጋጣሚ በቅርብ የማውቃት ሴት ናት። ‘ ኑ ጭቃ እናቡካ ’  የሚባል ፕሮጀክት ቀርፃ ብዙዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ራስዋን እያሳደገች ያለች ቅድም የጠቀስኩላችሁ ሳይንስ የገባት ምርጥ ኢትዮጲዊት ኢንተርፕረነር ነች።

እድሉን ካገኘሁ አንድ ቀን ይህንን ታሪኳንና እውቀቷን እንድታካፍላችሁ ለማድረግ እሞክራለሁ። ለዛሬ ግን ጭቃ ማቡካት ምን ፋይዳ ቢኖረው ነው የማህበራዊ ችግር መፍትሄ የሆነውና ቅድም ለጠቀስነው ሳይንስ ምሳሌ የሚሆነው የሚል ጥያቄ ሊነሳባችሁ ስለሚችል ይህንን ላካፍላችሁ። መልካም ንባብ።

የጭቃ ጨዋታ ለልጆች

የጭቃ ማቡካት ጨዋታ ለልጆች ያለው ሳይንሳዊ ጠቀሜታ ምንድነው?

በጭቃ እየተጫማለቁ ከህጻናት ጓደኞችዎ ጋር እየተጫወቱ ያሳለፉት የልጅነት ጊዜ ከነበረዎት በጣም ዕድለኛ ነዎት!

የጭቃ ጨዋታ ውድ የልጅነት ትዝታዎችን ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን ህጻናት እንዲማሩ፣ እንዲዝናኑ እና የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳ ጥሩ መንገድ ነው። ግን ከዚህ ያለፈ የጤና ጠቀሚታም አለው። በህጻናት ጤንነትና ስነልቦና ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የጭቃ ጨዋታ ለልጆች አካላዊ እና አእምሮአዊ ጤንነት ከፍተኛ ጠቀሚታ አለው። ይህ ቀደም ብሎም መጀመር ይቻላል። ነፍስ ላወቁ ልጆች ብቻ ሳይሆን አጠገባቸው ሆኖ የሚጠብቃቸው ሰው  ካለ ህጻን የሆኑ ልጆችም   እንኳን ከጭቃ ጨዋታ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

በጭቃ መጫወት ለልጆች በምን መልኩ ነው የሚጠቅመው?

ፅሁፌን ልቀጥል –

በመጀመሪያ ግን –

የጭቃ ማቡካት ጨዋታ ምንድነው?

ጭቃ ማለት ምናልባት እርስዎ የሚጠሉት ነገር ሊሆን ይችላል። ልጅዎ ጭቃ እንዳይነካ በየቀኑ ያስጠነቅቁትም ይሆናል። ነገር ግን የልጅዎን ልብስ ማጠብ ካልሰለቸዎ እና በጭቃ የመጫወት እድል ቢፈጥሩለት ልጅዎ ምን ጥቅም የሚያገኝ ይምስሎታል?

የጭቃ ጨዋታ ልክ እንደ የባህር ዳርቻ ላይ የአሸዋ ቅርጻ ቅርጽ የመስራት ጨዋታ ነው። የፈለጉት ቅርጽ በጭቃ መስራት፣ ማፍረስ፣ መልሶ ሌላ ቅርጽ መስራት – ለልጆች ፈጽሞ የማይሰለች ዓይነት ጨዋታ ነው። እርጥብ በመሆኑ ከጭቃ ጋር የሚደረግ እንቅስቃሴ ልብስን ከማቆሸሹ ውጭ ማለት ነው።

ልጆች ጭቃውን መጨፍለቅ፣ የተለያዩ ቅርጾችን መስራት፣ መቆፈር፣ መቆለል ወይም ጭቃ መግፋት ይችላሉ። እንዲሁም መዝለል፣ መበጥበጥ እና በጭቃ ውስጥ መንሸራተት ሊሆን  ይችላል። ይህም በሌላ በምንም ሊያዳብሩት የማይቸሉትን ያህል የፈጠራ ችሎታቸውን ያሳድግላቸዋል። ስለ ጭቃ አንድ በጣም ጥሩ ነገር በቀላሉ የሚገኝ መሆኑ ነው።

የጭቃ ጥቅሞች

በጭቃ ውስጥ ያሉ ጀርሞች በልጅዎ ጤና ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ስጋት ካደረብዎት፣ የማዮ ክሊኒካል ተማራማሪዎች በጭቃ ውስጥ መጫወት በብዙ መንገድ ለልጅዎ ጤናማ እንደሚሆን አረጋግጠዋል። ተመራማሪዎቹ ለልጆች የጭቃ ጨዋታ ከሚሰጥዋቸው ጥቅሞች የሚከተሉትን አካተዋል።

በሽታ የመከላከል አቅማቸውን ይጨምራላቸዋል

በጭቃ ውስጥ የሚገኙት ጀርሞች የልጅዎን በሽታ የመከላከል ስርዓት ለማጠናከር ይረዳሉ። እንዲያውም በልጅነታቸው ከጭቃ ጋር ንክኪ ያልነበራቸው ሰዎች እንደ አለርጂ እና አስም ላሉ በሽታዎች ሊጋለጡ ይችላሉ። ይህ ለልጅዎ ቀደም ብሎ የጭቃ ጨዋታ መጀመር እንዳልበት የሚጠቁም ተጨማሪ ምክንያት ነው። በመጀመሪያዎቹ 3 ዓመታት የልጅነት ጊዜ ውስጥ እስከ 50 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት የትንፋሽ እና ሌሎች ችግሮችን የሚያስከትሉ በሽታዎች ሊኖራቸው ይችላል። ለዚህ አንዱ መፍትሄ በተወሰነ ጊዜም ቢሆን የጭቃ ጨዋታ እድል እንዲያገኙ መፍቀድ ነው።

The Journal of Allergy and Clinical Immunology ላይ በወጣው ጥናታዊ ጽሁፍ እና እ.ኤ.አ. በ 2014 በከተሞች አካባቢ በሚኖሩ ትንንሽ ልጆች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ከ1 አመት ዕድሜያቸው በፊት ለቤት ውስጥ ጀርሞች የተጋለጡ ሰዎች ለአለርጂ የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው ። የጭቃ ጨዋታም ተመሳሳይ ጠቀሜታ እንዳለው ተጠቅሷል። የጭቃ ጨዋታ ትንሹን ልጅዎን እነዚህ ጠቃሚ ጀርሞች እንዲዋሃዱት የማድረጊያ አንዱ መንገድ ነው። ይላሉ ሳይንቲሰቶቹ። በ2016 እ.ኤ.አ. የተደረገ ሌላ ጥናትም በተመሳሳይ ይህንኑ አረጋግጧል።

የሆድ ውስጥ ጤንነት

የጭቃ ጨዋታ በሰውነት ውስጥ ያሉትን ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ብዝሃነት ለመጨመር ይረዳል። በፊንላንድ የተደረገ የህክምና ጥናት እንዳመለከተው በአፈር እና በእፅዋት ጊቢ ውስጥ የሚጫወቱ ሕፃናት ተፈጥሯዊ ቦታ ከሌላቸውና ቤት ውስጥ ከጭቃ ርቀው ከሚያድጉ ልጆች የበለጠ ብዙ ጠቃሚ የአንጀት ባክቴሪያዎች በሰውነታቸው ውስጥ አሉዋቸው።

አእምሮአዊ ጤንነት እና የፈጠራ ችሎታ

የጭቃ ጨዋታ ልጆች በዙሪያቸው ካለው ተፈጥሮአዊ ዓለም ጋር እንዲገናኙ እና እንዲዋሃዱት ያስችላቸዋል። በስሜት ህዋሳት ጨዋታ ልጆች የመዳሰስ ችሎታን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። የጭቃ ጨዋታ እና ሌሎች ከቤት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከቴሌቪዥን ስክሪኖች እንዲርቁ ብቻ ሳይሆን ለልጆች ንጹህ አየር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የፀሐይ ብርሃን የማግኘት እድልም ይሰጣቸዋል።

የጭቃ ጨዋታ ልጆች ፈጠራን (creativity)፣ ምናብን (Imagination)፣ በራስ መተማመንን  እና የቡድን ስራን እንዲያሳድጉ የሚረዳ የማስተማሪያ መሳሪያ ነው። እንዲሁም የግንባታ፣ የጥበብና እና የችግር አፈታት ክህሎቶችን ለማዳበር ይረዳቸዋል።

እንዲያውም አንዳንድ የስርዓተ ፆታ ተሟጋቾች የሥርዓተ-ፆታን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የጭቃ ጨዋታን እንደ ጠቃሚ የማስተማሪያ መሳሪያ መጠቀም እንዲሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ይህም የሆነው የጭቃ ጨዋታ ከኳስና መሰል ጨዋታዎች በተለየ ሁለቱም ፆታዎች በጋራና በእኩል የሚጫወቱት ጨዋታ በመሆኑ ነው።

ጥቂት ተጨማሪ ነጥቦች
  • ለልጅዎ በጭቃ የመጫወት እድሎችን መፍጠር በተለይ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ከሆነ ቀላል ነው። ይህ ካልሆነ ደግሞ ልጅዎ ጥልቀት በሌለው ባልዲ ውስጥ ወይም በትልቅ ጎድጓዳ ሳህን በረንዳ ላይ በጭቃ እንዲጫወት ማድረግ ይችላሉ።
  • ሁልጊዜ በጭቃ ጨዋታ ወቅት ህፃናትን እና ትናንሽ ልጆችን ይከታተሉ። በጣም ትንንሽ ልጆች ከሆኑ ጭቃ እንዳይበሉ ወይም ዓይናቸው ውስጥ እንዳያስገቡ ከመጠንቀቅ ውጪ ጨዋታው ጤናማ ነው፡፡
  • የልጅዎን ምርጫ ይጠብቁለት። አንዳንድ ልጆች በጭቃ መጨማለቁን ሊወዱት ይችላሉ።  ሌሎች ደግሞ ንፁህ ሆነው በጥንቃቄ መጫወትን ሊመርጡ ይችላሉ። ልጅዎ በምን ያህል ደረጃ ጭቃውን ማጨማለቅ  እንደሚፈልግ እንዲወስን ይፍቀዱለት።
  • የጭቃ ህጎችን ያዘጋጁ። ይህም በሌሎች ልጆች ላይ (ወይም በእናንተ ላይ) ጭቃ እንደማይወረውሩ የሚያስገነዝቡ መሰረታዊ ነገሮች ሊያካትት ይችላል።
  • ልጆችዎ በጭቃው ሳይሳቀቁ መጫወት እንዲችሉ ለጭቃ የሚሆን ልብስ ወይም ጋዋን ያልብሷቸው። 
  • አንዳንድ እቃዎችን ያቅርቡላቸው። እንደ ፕላስቲክ ኮንቴይነሮች ወይም ማንኪያዎች ያሉ ወይም ሌሎች ቅርጽ ለመስራት የሚያገለገሉ እቃዎች  በጣም ጥሩ ናቸው.
የጭቃ ጨዋታ እንቅስቃሴዎች

ከጭቃ ጨዋታ ጋር ሊደረጉ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች በጣም ብዙ ናቸው። ጥቂቶቹን እንይ፡-·       

  • ከጭቃ ዶናት እና ኩኪሶችን መቅረጽ።·       
  • የአሻንጉሊት ቤት ወይም ግንቦችን ለመገንባት የጭቃ ጡብ መስራት·       
  • የጭቃ ግንቦችን እና ህንፃዎችን መስራት·       
  • አሻንጉሊት መኪናዎችን በጭቃ መስራት·       
  • የተላያዩ የቤት እቃዎችን በጭቃ መስራት ለምሳሌ፦ ጀበና፣ ሸክላ ድስት፣ ባልዲ፣ ማንኪያ፣ ሳህን፣ ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ ወዘተ። ·       
  • የጭቃ ኳሶችን ከግድግዳ ወይም ከካርቶን ኢላማ ጋር እየወረወሩ መጫወት። ·
  • ሌሎችም እርስዎ ያልገመቱዋቸው የፈጠራ ስራዎች ልጅዎ ሲሰራ ሊያዩት ይችላሉ።
ማጠቃለያ

አሁን መጀምሪያ ወዳነሳነው ጥያቄ እንመለስ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለው ማህበራዊ ችግር ምንድነው?

የብዙ ከተሜ ሰዎች ችግር የሆነው ጭቃው ከየት ይምጣ? የሚለው ነው። የትስ ነው የሚቦካው? የምንኖረው ኮነደሚኒየም ወይም አፓርታማ! ልጆቻችን ጭቃ ሳያቦኩ ይደጉ? ያ ሁሉ ከላይ የዘረዘርነው በረከት ይቅርባቸው?

አይቀርባቸውም! እድሜ ለነሃመረ ዓይነት የገባቸው ኢንተርፕረነሮቸ ለሁሉም ዓይነት ችግር መፍትሄ አለው።

አንተም ገንዘብን ሳይሆን ችግርን አሳደህ ፈልግና የመፍትሄ ሰው ሁን። ያኔ ራስህን በሚሊየነሮች ተርታ ታገኘዋለህ።

አበቃሁ።

 

© ሙስጦፋ አብደላ

 

እንደተለመደው አስተያየታቸሁን እዚሁ አስታያየት መፃፊያው ላይ ፃፉልኝ። አመሰግናለሁ።

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *